Program in Amharic
መግቢያ
ኢሕአፓ (አንድነት) በነፃና ርቱዓዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሊመሠረት እንዲችል፣በኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ትግልና ሂደት ከፍተኛውን መስዋዕትነት የከፈሉት አባላቱ የወደቁለት ክቡር ዓላማ እውን እንዲሆን፣ተጠያቂነትና ግልጽነትን የተላበሰ ዴሞክራሲያዊ አሠራር በድርጅቱና በሀገራችን ውስጥ እንዲሰፍን እራሱን እንደገና መርምሮና መዋቅራዊ መሻሻሎችን አድርጎ፣እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባውን ቃል ኪዳን ዳግም አድሶ፣በአዲስና በተሻለ አሠራር ትግሉን ቀጥሏል።
ኢሕአፓ ከተመሠረተበት ከሚያዝያ 1964 ዓ. ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ እኩልነት የሰፈነባትና ዜጎች በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩባትሉዓላዊነቷን የጠበቀች ሀገር በሁሉም መስክ ለመገንባት የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር ታግሏል፤ አታግሏል፤አሁንም እየታገለ ይገኛል። ኢሕአፓ ከምሥረታው ማግሥት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን ሦስት አገዛዞችን አጥብቆ የታገለ ሲሆን ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱም አገዛዞቹ የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት ረግጠውና አፍነው በአምባገነንነት የቀጠሉ መሆናቸውና ጨርሶም ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸው ነው። በተለይም ዛሬ በሀገራችን ለሥልጣን የበቃው ገዥ ሃይል ጠባብ ብሄረተኛ በመሆኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሄረሰብ ከፋፍሎና አናክሶ ሊገዛ ይሁነኝ ብሎ የወሰነ አምባገነን ቡድን ነው። ይህ ቡድን በሥልጣን እስካሁን የቆየው በሕዝብ ድጋፍ ሳይሆን የወታደራዊና የደህንነት ኃይሉን በመጠቀም ተቃውሞን በኃይል እያፈነ በመቀጠሉ ነው። የጥፋት ዓላማውን ከማሳካት ያደናቅፉኛል ብሎ የገመታቸውን እንደ ኢሕአፓ ያሉ ድርጅቶችን ሕጋዊ ሆነው እንዳይንቀሳቀሱ በማገድ ተልዕኮውን ከግቡ ለማድረስ ጥሯል፤ አሁንም በመጣር ላይ ይገኛል። በ1997 ዓ. ም የግንቦቱ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገዛዙን ከቶም እንደማይፈልገው ድምፁን በመንፈግ ቢያረጋግጥም ቡድኑ ልዩ የፀጥታ ኃይሉን አሰማርቶ ሕዝቡን በመጨፍጨፍ በኃይል መግዛቱን ቀጥሏል። ይኸው ጠባብ ብሄርተኛ አገዛዝእንዲለወጥ፣ የሕዝብን ድምፅ እንዲያከብር፣ የሰላምና ዕርቅ መንገድ እንዲመርጥ በተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጎለት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በማንአለብኝነትእንደቀጠለ ነው። እንዲያውም አገዛዙ በሕዝብ ላይ የሚያደርስውን አመጹንና አፈናውን በማጠናከርና የሀገሪቱን ማንኛቸውም ተቋማት በማፈኛ መሣሪያነት በመጠቀም የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ለመብታቸው የታገሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለእሥር ዳርጎ በአምባገነንነቱ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለፍጹም አምባገነን፣ዘረኛና አሸባሪ አገዛዝ ሰለባ መሆን የለበትም።ስለሆነምይህንን አስከፊ አገዛዝ፣ኢትዮጵያውያን ተባብረውና በማንኛውም መንገድ ታግለው፣ ሊያስወግዱት እንደሚገባ ኢሕአፓ (አንድነት) በፅኑ ያምናል። ........