Menu
Super User

Super User

ሸንጎ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚያገለግለውን አመራር መረጠ

 

በኦታዋ ካናዳ በተካሄደው ጉባኤ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2012 የተመሠረተውና የኢትዮጵያ የአንድነት ኃይሎች ትልቁ ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ፣ (ሸንጎ) በዛሬው ዕለት ባካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ድርጅቱን የሚመሩ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።

በዚህም መሰረት ከስራ አስኪያጅ ኮሚቴው አባላት ውስጥ ዶክተር ታዬ ዘገዬን፣ ሊቀመንበር ወይዘሮ ጽጌረዳ ሙሉጌታን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ግደይ ዘርአጽዮንን ዋና ጸሀፊ እና አቶ መሐመድ ጀሚልን ምክትል ዋና ጸሀፊ አድርጎ መርጧል፡፡ የተቀሩት የኮሚቴው አባላት ደግሞ የተለያዩ የተግባር ኮሚቴወችን በኃላፊነት ይመራሉ።

ሸንጎው በቅርቡ አጠቃላይ ጉባዔ በማካሄድ ኢትዮጵያችንና ሕዝቧ የሚገኙበትን ሁኔታ በጥልቅ ከመረመረ በኋላ ሀገራችን ከምትገኝበት አስከፊና አደገኛ የግፍ ሥርዓት ተላቃ አንድነቷ ተጠብቆ እኩልነት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም የህግ የበላይነት ወደ ተከበረበት ለሁሉም ዜጎቿ የሚሆን ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስችለውን ለውጥ እውን ለማድረግ መደረግ በሚገባቸው መሠረታዊ ጎዳዮች ላይ የትግል አቅጣጫ ነድፏል።

ይሀ አሁን የተመረጠው የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ብቻ ሳይሆን በአንድነት ኃይሎችም ላይ የተነጣጠረውን ጥቃት በመመከትና የአንድነት ኃይሎችን በማጠናከር የሕዝባችን የነፃነት ራዕይ እውን እንዲሆን ለማስቻል ከፍተኛ አደራን ተቀብሏል።

ይህን ለማድረግም ከባዕዳን ተጽእኖ ነፃ ሆኖ ራሱ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ያማከለና መሠረት ያደረገ ትግልን አጠናክሮ ይቀጥላል።

የሸንጎው የጋራ አቋሞች:-

  • በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት በሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትና ሉዓላዊነት ላይ የማያወላውል እምነት
  • ፍትህ የሰፈነበትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጸንቶ መታገል
  • ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቹ መከበር አለባቸው ብሎ ማመን
  • በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት አድሏዊነት እንዳይኖርና ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሕግ ፊትና በሶሻልና የፖለቲካ ነፃነታቸው እኩል ዜጎች መሆናቸውን በተግባር ማረጋገጥ
  • የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስትና አገዛዝ ሥርዓት የአፈናና የጭቆና ሥርዓት በመሆኑ መለወጥና በህገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት መተካት እንዳለበት መቀበል

የሚሉት ሲሆኑ እነዚህን መሠረታዊ መተክሎች የሚቀበል ማንኛውም ግለሰብ፤ ስብስብ ወይም ድርጅት ሸንጎውን በመቀላቀል ወይም በጋራ በመሥራት ሕዝባችንንና ሀገራችንን በጋራ እንድንታደግ ጥሪያችንን በድጋሜ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

ብሄራዊ መግባባትና መልካም አስተዳደር “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” መሆን የለበትም!!

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አስከፊ ሁኔታ ቀይሮ አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው ከፍራቻና፣ ከሰቆቃ ተላቆ መብቱ ተረጋግጦ ፣ እንዲኖር እነሆ ትግሉን ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ይህን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግም ህዝብን ያማከለ፣ ሰላማዊ፣ ትግል የማካሄድ፣ አስፈላጊነትን አምኖ ይሀንኑም በራእይ ደረጃ አስቀምጧል። ከዚህም አልፎ ታቃዋሚው በሀገር ቤት ወይም በውጭ ሀገር የሚገኝ በሚል አላስፈልጊ ክፍፍል ወይም መሰረታዊ ባልሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በማተኮር ራሱን እና አጠቃላይ ትግሉን ከሚጎዳ አካሄድ ተቆጥቦ፣በጋራ ለመቆም የሚያሰችለው የትግል አንድነት እንዲፈጥርና አቅሙንም እንዲገነባ  ደግመን  ደጋግመን አሳስበናል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሽንጎ ትልቁ የአንድነት ሀይሎች ስብስብ ቢሆንም አሁንም ገና ወደአንድ ጎራ ሊሰባሰቡ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ድርጅቶች፣ስብሰቦችና ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው። ይህን ሃይል አሰባስቦ አይበገሬ ያንድንት ሀይል መፍጠርና ትግሉን ማፋፋም፣ እያደር ወደተወሳሰብ ጎዳና በማምራት ላይ የምትገኘውን ሀገራችንንና ህዝባችንን ለመታደግ ዋነኛው መሳሪያ ነው። ይህ መሰረታዊ ዋሰትና ሳይዘገይ ተግባራዊ እንዲሆንም አሁንም ሳንታክት ጥረታችንን እንቀጥላለን።

የትግላችን  ራእይ የግፍ እና የኣድልኦ ስርአት አክትሞ፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብአዊ መብት፣ የሁሉም ዜጋ የግልና የጋራ መብት የሚከበርበት በሁሉም ባለድርሻዎች ሙሉ ተሳትፎ የዳበረ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን እውን ማድረግ ነው።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው እና ባለፈው ነሀሴ ባካሄደው ጉባኤው እንዳጸደቀውም፣ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት፣ የሁሉንም ዜጎች አወንታና ታአማኒነትን ያገኘ ስርአት ለመመስረት ሀገራችን ያላት አማራጭ በብሄራዊ መግባባትና በብሄራዊ እርቅ ጎዳና መጓዝ ነው።

ይህ ሂደት ካግላይነት የተላቀቀ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ፣ የሁሉንም ድምጽ ለማዳመጥ፣ የቆረጠ፤ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ የሚያስችል መሆን ይገባዋል። በኛ አመለካከት ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ የተወሰኑ ክፍሎች ወይም ድርጅቶች ከደረሰባቸው ውጥረት ለመወጣት የሚጠቀሙበት የጊዜ መግዣ ታክቲክ ሳይሆን በሀገራችን ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ማሀበራዊና ሌሎችንም ችግሮቻችንን ፊት ለፊት በጋራ መርምረን በአርቆ አሳቢነት፣ በብሰለትና፣ በመቻቻል፣ በወንድማዊና እህትማማች ስሜት፣ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት  የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ እውነተኛ ጉዞ ነው መሆን ያለበት።

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለዘላቂ ሰላም፣ ለልማት፣ ለምንመኛት ታላቅ የበለጸገች ኢትዮጵያ መሰረት የምንጥለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ አላስፈልጊ ደም መፋሰስን፣ የእርስ በርስ መጠፋፋትን ፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ጽንፈኛነትን፣ ቂም በቀልን አስወግደን ከራሷ ጋር የታረቀች ፣ የጦርነት አዙሪትን የሰበረች ከውጭ ሊሰነዘር ለሚችል ጥቃት ያልተጋለጠች ፖለቲከኞች ከስልጣን በተወገዱ ቁጥር፣ለእስር ወይም ለስደት የማይዳረጉባት ንብረታቸው ከሀግ ውጭ የማይነጠቅባት፣ሀገርና፣የፖለተካ ስርአትን ለመመስረት የሚያሰችል መሰረት የምንጥለው።

በዚህ አንጻር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ መሪ ጠቅላይ ሚኒሰተር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የነጻ ፕሬስን መብት ለማክበርና ከተቃዋሚዎች ጋር በሀገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ፍላጎት እንዳለቸው ፣ሌሎችም በህጋዊነት እንዲንቀሳቀሱ ሲሉ ተናግረዋል።

በሸንጎው አመለካከት አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የችግሩ አንዱ አካልና ዋናው መሠረት በመሆኑ የሀገራችንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለብቻው ሊቀይረው ከቶውንም አይችልም፡፡ እንዲያውም አሁን ባለው መልኩ እየቆየ በሄደ ቁጥር የሚወስዳቸው እርምጃወች ችግሩን ወደባሰ መወሳሰብ ያሳድገዋል። በሀገራችን ውስጥ  ጎልተው ከሚታዩት ብሶቶችና ጥያቄዎች አንጻር ሲታይ አንድ ድርጅት በተናጠል ልዩ  መፍትሄ አምጥቶ ሁሉንም ሊያረካ አይችልም።ይህ ቢሆን ኖሮ የህወሀት/የኢህአዴግ የ24 አመታት ጉዞ የኢትዮጵያን ችግር በፈታው ነበር።

የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች በትክክል መረዳት እና  መቅረፍ የሚቻለው ለጥቂት ሰአታት በጠባብ አጀንዳ ላይ ለተቃዋሚዎች ገለጻ በመስጠትና  በገዥው ቡድን እቅድ ላይ “ሀሳባችሁን አካፍሉን “ ወይም “ወደሀገር ተመልሳችሁ ስሩ” ከሚል ንግግር ባሻገር ሁሉንም አሳታፊና እውነተኛ  በሆነ ብሄራዊ መግባባትን እውን ሊያደርግ በሚችል ሂደት ነው።

በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አይነት  የተወሳሰበ ችግር መፍታት የሚቻለው አንዱ መፍትሄ ሰጭ ሌላው ደግሞ መፍትሄ ተቀባይ በሚሆኑበት አካሄድ ሳይሆን ሁሉም የችግሮቹ ባለቤት ሁሉም ደግሞ የመፍትሄዎቹም ባለቤት ሲሆኑ ነው። የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች  መፍታት የሚቻለው ፍትህን፣ መተማመንና፣ አርቆ አሳቢነትን መሰረት አድርጎ ያለፉ ችግሮች እንደገና እንዳይደገሙ ምን መደረግ እንዳለበት  ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ተነጋግሮ መግባባትና መስማማት ላይ መድረስ ሲቻል ነው።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦታ ሊኖራት ይገባል፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያው ቅሬታ፣ የሚደመጥባት፣ መፍትሄም የሚፈለጋባት ልትሆን ይገባል። ኢትዮጰያ በዜጎቿ መካከል የበኩር ልጅ እና የእንጀራ ልጅ የሚባለው አይነት አድልኦ ለማስተናገድ የማትመች መሆን አለባት።ኢትዮጵያ አንዱ ሌላውን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣ ከቻላችሁ ሞክሩን” የሚባልባት ሀገር መሆን የለባትም።

ይህን እውን ለማድረግም ማንንም ያላገለለ ሁሉም ባለድርሻዎች በሚሳተፉበት የብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ሂደትን እውን ማድረግ ይጠይቃል።ይህ ሂደት ድፍረትን የሚጠይቅ ነው። ሀገሪቱንና ህዝቧን አሁን ወደሚገኙበት ውስብስብ ሁኔታ ካደረሳቸው አካሄድ መላቀቅን የግድ ይላል። ይህ ሂደት በዜጎች መካከል ፣ በተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል፣ ወዘተ እምነትን መገንባትን እና እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ያሁኑ “ጥሪም” የፖለቲካ ጊዜ መግዣ  አለመሆኑን ማረጋገጥን ይጠይቃል። ይህን ሁኔታ የሚጠይቀውን የመተማመን መሰረት ለማጣል ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁትን የፖለቲካ እስረኞች ጋዜጠኞች ወዘተ መፍታት ለነጻ ፕሬሱና አሁን በህጋዊነት ተመዝግበው በመስራት ላይ ለሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የመፈናፈኛ ሜዳውን ማመቻቸት አንድ ታላቅ እርምጃ ይሆናል።

ይህ ባልሆነበት “ኑ ተሳተፉ;  ምክክር እናድርግ” ማለቱ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” በሚለው በሀገራችን ብሂል የሚገለጥ ይሆናል።ይህ ደግሞ የሀገራችንን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ይበልጥ ያባብሰዋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

በወገኖቻችን ላይ የሚካሄደው አፈናና ጭፍጨፋ ባስቸኳይ ይቁም

በPDF ለማንበብ ይህን ይጫኑ

በአለፉት  ሳምንታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በመሀል፣  በምእራብ፣ ምስራቅና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጽያ የስርአቱን ፖሊሲዎች በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ተማሪወች በገዥው ወያኔ ኢህአዴግ ጸጥታ ሀይሎች መደብደባቸው፣ መታሰራቸውና በጭካኔ መገደላቸው በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች በመገለጥ ላይ ነው።

ወያኔ ኢህአዴግ ላለፉት 24 አመታት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ሰላማዊ ተቃውሞን በሀይል ለማፈን መሞከሩ በሀገራችን ውስጥ አላስፈላጊ የሆነ መካረርን ከማስከተሉም በላይ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች እጅግ ወደተወሳሰበ ደረጃ ያደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ በገዥው ቡድን ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለዘመድ አዝማድ  እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ የተሰማውን  ሀዘን እየገለጠ በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር ሁሉም ኢትዮጽያውያን የሚያካሂዱትን ትግል በጉልበት ለማፈን የሚደረገውን ሙከራ ሁሉ በጥብቅ ያወግዛል።

የሀገራችን ዘርፈብዙ ችግሮች በትእግስት፣ በመደማመጥ፣ ባርቆ አሳቢነትና ለህግ በመገዛት እንጂ በጉልበትና ባፈና ሊፈታ እንደማይችል ገዥው ቡድን ሊገነዘብ ይገባዋል። ትላንት ከትላንት ወዲያ እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም የዜጎችን ደም በማፍሰስ በማሰርና በማሰፈራራት ተቃውሞን አፍኖ የስልጣን እድሜን ለማራዘም መሞከር እጅግ ሀላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፣ ፈጽሞ ማስተዋል አለመቻልም ነው። ገዥው ቡድን በህዝብ ላይ የሚያካሂደው አፈና ሁሉ እንዳልሰራ በተገነዘበ ቁጥር እጅግ ዘግናኝ ወደሆነ ተጨማሪ ተግባር እያመራ ይገኛል። አሁን ያለው ሁኔታ ወገኖቻችንን በገዥው ቡድን የጸጥታ ሀይሎች እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ያመላክታል።

በድጋሚ የስርአቱ መሪዎች ከዚህ የወንጀል ተግባር እንዲታቀቡ ፣ በህዝብ ላይ ለደረሰው ጭፍጨፋና ስቃይ ተጠያቂ የሆኑ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እያሳሰብን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አንዱ ዜጋ ሲነካ ሁሉም እንደተነካ በመገንዘብ የስርአቱን የግፍ እርምጃ በጋራ እንዲያወግዙና በጋራ እንዲቋቋሙ ከማንኛውም ጎራ ለሚመጣ የከፋፋይ ሴራ ሰለባ እንደይሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የተቃወሚ ድርጅቶችም ሆኑ የሲቪክ ማህበራትም ታራ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ከመሯሯጥ ይልቅ ሀገራችንና ህዝባችን ያሉበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ተገንዝበው የህዝባችንን አንድነት አጠናክሮ የሀገራችንን ደህንነት አደጋ ላይ ሳንጥል የስርአት ለውጥ ለማምጣት የህዝባችንን ትግል ማቀነባበር የሚቻልበትን መንገድ ባስቸኳይ ለመፈለግ በጋራ እንድንነሳ የትብብር ጥሪያችንን በድጋሚ እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

 

 

Subscribe to this RSS feed