Menu

የኢሕአፓ (አንድነት) ስምንተኛው ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ

የኢሕአፓ (አንድነት) ስምንተኛው ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (አንድነት)፣ ኢሕአፓ (አንድነት) ከሰኔ ፳፬ እስከ ሰኔ ፳፰ ቀን ፪ ሺህ ፲ ዓ. ም (July 1 - 4, 2018) ድረስ በሰሜን አሜሪካ፣ በዳላስ ከተማ ስምንተኛውን ድርጅታዊ ጉባዔ አካሂዶ በተሳከ ሁኔታ አጠናቅቋል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ አባላት ከተለያዩ ክፍለዓለማት በውክልና የተገኙበት ሲሆን የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ በሰፊው ከመረመሩ በኋላ ጉባዔው የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

•ስምንተኛው ጉባዔ በድርጅቱ አመራር የቀረበውን ዘገባ በጽሞና ካዳመጠና ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ አንዳንድ ግብዓቶችን ጨምሮ ዘገባውን ያለ ምንም ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ተቀብሏል።
•አሁን አገራችን ውስጥ የሚታየውን ሕዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተሰፋና ስጋቱን፣ ከዓለምና አካባቢያዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ስምንተኛው ጉባዔ በሰፊው ከመረመረ በኋላ ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ ለመሠረታዊ ለውጥ ለመታገል ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሷል።
•ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ውስጥ ሕዝባዊ እምቢተኛነቱ በፈጠረው ጫና የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሊደገፍና ሊበረታታ እንደሚገባው ጉባዔው አምኖበታል። የለውጥ እንቅስቃሴው ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አገዛዙ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያደረሰውን ጥቃት በመቃወም ከዳር እስከዳር ገንፎሎ በመነሳት እያሳየ ያለው የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ኢትዮጵያዊነት እንደገና እንዲያንሰራራ የፈጠረውን መንፈስ የኢሕአፓ (አንድነት) ጉባዔ በሙሉ ልብ የሚደግፍና የሚያበረታታ መሆኑን አስረግጦ፣ ይህ መንፈስ የመጨረሻ ግቡን እንዲመታ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ ወስኗል።

•በአገራችን ውስጥ ያንሰራሩትን ብሄራዊ የፖለቲካና የማኅበራዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትንና ዘላቂ ሰላምን ዕውን ለማድረግ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያሳትፍ ብሄራዊ ጉባዔ መጥራት ሁኔታው የግድ የሚለው በመሆኑ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን የኢሕአፓ (አንድነት) ጉባዔ ይጠይቃል። ለተግባራዊነቱም የራሱን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

•አገራችን አሁን የይቅርታና የመደመር አየር የሚስተጋባበባት መድረክ ሆናለች። ይህ የመደመር መርህ መሠረት በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች ለአገራቸው ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ሲባል ልዩነታቸውን አጥብበው በጋራ መሥራት አለባቸው ብሎ ኢሕአፓ (አንድነት) ያምናል። በዚህ መሠረት ጉባዔው የኅብረት ትግልን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ኢሕአፓ ጥረት ያደረገባቸውንና የተሳተፈባቸውን የኅብረት ትግሎች በሰፊው መርምሯል። ስለሆነም አሁን በመሬት ላይ ያለው ሃቅ በኅብረት መታገል ውጤታማና ተስፋ ሰጭ ስለሆነ ኢሕአፓ (አንድነት) እስካሁን ሲከተለው የነበረውን በኅብረት የመታገል አቋሙን በማደስና በማጠናከር ከኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ) ጋር በመሆን ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠና ሌሎችንም ሊያሳትፍ በሚችል ጥንካሬ ለዴሞክራሲና ለሀገር ሉዓላዊነት የሚደረገውን ትግል አጠናክሮ ለመቀጠል ጉባዔው ወስኗል።

•ጉባዔው የቀድሞ አባሎችን በሚመለከት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ከሌላኛው የኢሕአፓ ክፍል ጋር ተነጋግሮ እንደ ድሮው ኢሕአፓን አንድ አድርጎ ለመሥራት ወስኗል። ይህንን የስምንተኛውን ጉባዔ ውሳኔ አስመልክቶ ደብዳቤ በቀጥታ ለኢሕአፓ ለማቅረብ ወስኗል።
•ህወሓት በረሃ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያን ለማፈራረስና የአምባገነን አገዛዙን ለራሱ በሚያመች መንገድ በሕዝባችን ላይ ለመጫን አቅዶና ሰንቆ ያመጣውን ሕዝብን ከፋፍሎ ለመግዛትና ኢትዮጵያዊነትን የሚያኮስምነውን የፌደራል አወቃቀር ጉባዔው በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ይህን አገር

የሚያፈራርስና ሕዝባችን እርስ በእርሱ የሚያፋጅ የአገዛዝ ስልት በሙሉ ድምጽ ውድቅ አድርጓል።

•ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ የአመራር አባሎቻችን በሜዳና በከተማ በህወሓት ታፍነው ተወስደው ላለፉት 27ና ከዚያም በላይ ዓመታት የት እንደደረሱ አይታወቅም። ስለዚህ መንግሥት ታፍነው የተወሰዱ አባሎቻችንን መዳረሻ እንዲያሳውቀንና በሕይወት ያሉትንም በተሰጠው የምህረት አዋጅ መሠረት ከእስር እንዲለቀቁ ጉባዔው በሙሉ ድምፅ ጠይቋል።

•በድርጅቱ አባላት ተጠንቶ የቀረበውን የፌደራል አወቃቀር በሰፊው መርምሮ መጨመር አለባቸው ብሎ ያመነባቸውን ጠቃሚ ግብዓቶች ጨምሮ ጥናቱን ላቀረበው ኮሚቴ ተሰጥቷል። የመጨረሻውን የተጠናቀቀ ሰነድ በ15 ቀናት ውስጥ ለአባላት እንዲያቀርብ ጉባዔው ለኮሚቴው መመሪያ ሰጥቷል።

•ጉባዔው ቋንቋን በሚመለከት ሰፊ ውይይት አካሂዷል። ብሄረስቦች የአካባቢያቸውን ቋንቋ እንዲጠቀሙ፣ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ የሚለውን የቆየ የድርጅቱን አቋም አሁንም የበለጠ አጠናክሮ አፅድቆታል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ኦሮምኛ በአገራችን ውስጥ በርካታ ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ በመሆኑ፣ ከአማርኛ በተጨማሪ ሁለተኛ የሃገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ጉባዔው ወስኗል። የመጻፊያ ፊደልን በተመለከተ ከላቲን በተሻለ የግዕዝ ፊደል ኦሮምኛን ይገልጸዋል ብሎ ጉባዔው ስላመነ የግዕዝ ፊደል የኦሮምኛ የመጻፊያ ፊደል እንዲሆን ወስኗል።

•በመጨረሻም ከሰባተኛው ጉባዔ ጀምሮ በማገልገል ላይ የቆዩትን የአመራር አባሎችን አመስግኖ በእነሱ ቦታ አዲስ የድርጅቱን ከፍተኛ አመራር አባላትንና የአባላት መብት አስጠባቂ ኮሚቴን በመምረጥ ጉባዔው ተጠናቋል።

ሐምሌ ፭ ቀን ፪ ሺህ ፲ ዓ. ም July 12, 2018

More in this category: « እንኳን ደስ ያለን!
back to top