Menu

አገራችን ወደከፋ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባች ነው!

ቅጽ 45 ቁ.2                                                                         ግንቦት 2009

አገራችን ወደከፋ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባች ነው!
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተሚያ ጀምሮ ዓለማችን ርዕዮተ-ዓለምን መሠረት ባደረጉ ሁለት ጎራዎች ተከፍላለች። የምዕራቡ ክፍለ-ዓለም በኃያሏ አሜሪካ መሪነት ወደ አንድ ጎራ ሲሰባሰብ፣ የምሥራቁ ክፍለ-ዓለም ደግሞ በዚያን ጊዜ ኃያል በነበረችው በሶቪዬት ኅብረት ዙሪያ ጎራውን ለይቶ ቆመ። አወሮጳም በዚሁ ምክንያት ድንበር ተከልሎላት ምዕራብና ምሥራቅ ተብላ ተከፈለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሁለት ከፍተኛ የወታደራዊ ቃል ኪዳን ድርጅቶች ተመሠረቱ። በምዕራቡ ዓለም የሚመራው ኔቶ (NATO) ተብሎ ሲሰየም፣ በምሥራቁ ጎራ ያለው ደግሞ በሶቪዬት ኅብረት መሪነት ዋርሶ (WARSAW) ተብሎ ተሰየመ። አርባ አምስት ዓመታት በቆየው በዚህ የክፍፍል ወቅት ሌሎች ሁኔታዎችም ተከስተዋል። ለምሳሌ በርካታ የእስያና የአፍሪቃ አገሮች ከቅኝ-ግዛትነት ተላቀው ነፃ አገሮች ሆነዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ የእርስ በርስ ጦርነቶች በመካሄዳቸው፣ ሁለቱ ኃያላን አገሮች በጦር መሣሪያ እሽቅድድም ውስጥም ገብተው ነበር። በተጨማሪም፣ ሁሉም ተከታይ አገሮቻቸውን ለመከላከል ሲሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ገብተዋል። ለዚህም ትልቁና ጎልቶ የሚታወሰው የቬትናም ጦርነት ነው።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ አገሮች ተሰባስበው ሊመክሩበት የሚገባ መድረክ በማስፈለጉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ማዕከል እንዲቋቋም ሆኗል። ይህ ድርጅት እስካሁን ሁለት ከፍተኛ ወታደራዊ ስምሪቶችን መርቷል፣ እነዚህም በኮሪያና በኮንጎ የተካሄዱት ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የሚያመረቃ ሥራ ሠራም አልሠራም ብዙ ዓለምአቀፍ የፀጥታ ማስከበር ተግባራትን በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት አከናውኗል፣ አሁንም እያከናወነ ነው። የፀጥታ ማስከበር ተልዕኮው በአብዛኛው በሦስተኛው ዓለም አገሮች መካከል የሚደረጉ ግጭቶችን ለማብረድ የተደረገና እየተደረገም ያለ ጥረት ነው።

ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ በሶቪየት ኅብረት በተደረገው የዕርዮተ-ዓለም ማፈግፈግ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ብዙ ሁኔታዎች በመለዋወጣቸው ዛሬ ዓለም በምዕራቡ ኃያል አገር በአሜሪካ አመራር ሥር ወድቃለች፣ ብዙ አዳዲስ አገሮችም በመፈጠራቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች ቁጥር ወደ 192 ከፍ ብሏል። አዲስ በተመሠረቱ አገሮችም ሆነ በነባር የሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ከፍተኛ የሕዝብ እልቂትና እንግልት እንዲሁም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ ፍልሰትና ስደት ተከስቷል። የዓለም የኃያላን አገሮች ሚዛን በመዛባቱም የሦስተኛ ዓለም አገሮች ለባሰ ችግር እንዲጋለጡ ሆነዋል።
ከዓመታት በፊት በቱኒዚያ ተጀምሮ በርካታ የዐረብ አገራትን ያጥለቀለቀው የዐረብ “የፀደይ ንቅናቄ” የተሰኘው አብዮት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ቦታ ይዞ ይገኛል። በዚህም ሳቢያ መሪዎች ለረዥም ጊዜ ከተቆናጠጡበት ሥልጣናቸው እንዲወገዱ ሲሆን፤ የተወሰኑትም ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህንን ተከትሎ የተጫሩ የእርስ-በርስ ጦርነቶች እስካሁን ድረስ እየተካሄዱ ይገኛሉ። ይሁንና ንቅናቄው በተጫረባቸው አገራት ሁሉ ሕዝባዊ ፍላጎቱ ግቡን አልመታም። ለምሳሌ በሶሪያ ውስጥ የተፈለገውን ውጤት አላመጠም። እንዲያውም ሶሪያ ወደማያባራ ከፍተኛ የእርስ-በርስ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ሆናለች። የብዙ ሰዎች ሕይወትም እየተቀጠፈ ነው። ሩሲያ በሥልጣን ላይ ያለውን የሶሪያን መንግሥት ደግፋ በመሰለፏ ሁኔታው ይበልጥ ተወሳስቦ፣ አዲስ የሶሪያ፣ የፋርስ፣ የሊባኖስና የሩሲያ ግንባር ተፈጠረ። የዚህ ግንባር መፈጠር ከልዕለ-ኃያሏ ከአሜሪካ ጋር ደግሞ ከፍተኛ ፍጥጫ ፈጥሯል።
በሳውዲና በካታር የሚደገፈው በካሊፍ የሚመራው የእስላምና አክራሪ ቡድን (ISIS) በአንድ ጀምበር ከፊል ሶሪያንና ኢራቅን ተቆጣጠረ። ይህ አክራሪ ቡድን በወቅቱ ሊቢያ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው አሰቃቂ የግፍ ግድያ ምንጊዜም የሚረሳ አይደለም። ቡድኑ ዋነኛ መሠረቱ በሶሪያ፣ በፋርስና በሊባኖስ ለተፈጠረው ሒዝቡላ ለተሰኘው ሌላው አክራሪ የጥፋት መልዕክተኛ ግንባር ተፃራሪ ኃይል ሲሆን፣ ሁኔታውን ልዩ ያደረገው ግን በኃያላኑ፣ ማለትም በሩሲያና በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ኃይል ከተፃራሪዎች ጎን መቆማቸው ነው። ይህ የተወሳሰበ ዓለም-አቀፍ ሁኔታ ለብዙ አገሮች ስጋትና ችግር ሆኗል።
የመን ላይ ጦርነት ለመክፈት የተቋቋመው የሳውዲ ግንባር፣ አጎራባች አገሮችንም አካቷል። የዚህ ግንባር አባል የሆነችው ካታር አሰብ ወደብ ላይ ወታደራዊ አምባ መሥርታለች። የግንባሩ ሌላ አባል የተባበሩት ዐረብ ኤምሪትስም ሶማሌ ውስጥ በርበራ ወደብ ላይ ወታደራዊ አምባ ይዛለች። ሳውዲ ዐረቢያም እንዲሁ ወታደራዊ መወንጨፊያ ማዕከል ጅቡቲ ላይ አቋቁማለች። በግብፅ አነሳሽነት ከኡጋንዳ ቀጥሎ ከደቡብ ሱዳን ጋር የተፈጠረው ወዳጅነትም በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ግልጽ ነው። በቅርቡ የአሜሪካንን ድጋፍ አግኝተው የሱማሌ ፕሬዘደንት የሆኑት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ፋርማጆ በቅድሚያ ወዳጅነታቸውን ያረጋገጡት ለሳውዲ ዐረቢያ ነው። ከነዚህ ሁኔታዎች ተነስተን አገራችንን ኢትዮጵያን ስንቃኝ፣ ያለምንም መፈናፈኛ በዐረብ ሊግ ወታደራዊ ቀለበት ውስጥ የገባች አገር መሆኗ በግልጽ እናያለን።
የኢትዮጵያ ችግር ከጥንት ጀምሮ ምንጩ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የአገራችን መልክዓ-ምድር አቀማመጥና የዓባይ ወንዝ ባለቤት መሆኗ ነው። ኢትዮጵያን በዓረቦችና በምዕራባውያን ዓይን ውስጥ እንድትገባ ያደረጓት ያው የቀይ ባህርና የዓባይ ወንዝ ናቸው። በሚቀጥሉት መቶ ዓመታት ውስጥ የዐረብ አገሮች አሁን ያላቸው ውሃ እንደሚያልቅ ወይም እንደሚደርቅ የሳይንስ ተመራመሪዎች ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የዓባይን ወንዝ በጎላን ሃይት አሻግረው ለመጠቅም ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ይህን ለማሳካትም የተዳከመችና የተከፋፈለች፣ በነሱ ቡራኬ ሥር የምትተዳደር ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር ይፈልጋሉ። ይህን ዕቅድ ደግሞ የምዕራብ አገሮች ከኋላ ሆነው ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ቀደም ሲልም እንደዚሁ እንግሊዝ፣ ሱዳንንና ግብፅን በቅኝ-ግዛትነት ስትገዛ በነበረበት ወቅት፣ ያለ ኢትዮጵያ እውቅና የዓባይን ወንዝ በባለቤትነት ለሱዳንና ለግብፅ አፈራርማ ማስረከቧ የሚዘነጋ አይደለም። ቱርኮች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር ከፍተኛ ሙከራ ያደረጉት ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች ለማሳካት እንደሆነም ከታሪክ እንረዳለን። ግብፅም ብትሆን በሰሜን፣ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል አገራችንን ለመያዝ ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርጋለች። ስለዚህ ዛሬም እንደድሮው በምዕራቡ ዓለም አበረታችነት የኢትዮጵያን ዙሪያ መክበባችው የሚያስረዳን ነገር ቢኖር ይህንኑ ሃቅ ነው። የህወሓት ቡድን አልሞና አቅዶ ያመጣው ዓላማ ተሳክቶለት ዛሬ ኢትዮጵያ ወደብ-አልባ ሆናለች። አሁን የምትጠቀመው የጅቡቲን ወደብ ተከራይታ ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጀቡቲ የብዙ ኃያላን አገሮች የጦር መደብር ስትሆን፤ ወደብ አስተዳዳሪዎች ደግሞ ዐረቦች ሆነዋል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ ልንገነዝብ ይገባል። ስውር ደባው ይህ ከሆነ እነዚህ ወደቡን የሚያስተዳድሩት ዐረቦች ኢትዮጵያን ከብዙ በጥቂቱ በሚከተሉት መንገዶች ሊጎዷት ይችላሉ ተብሎ ይታምናል። እነዚህም፦ 1ኛ) የወደቡን ኪራይ ከአቅም በላይ ከፍ ማድረግ፣

2ኛ) በዕቃዎች ላይ የቀረጥ ዋጋ በመጨመር ኢትዮጵያ ውስጥ የሸቀጦች ዋጋ ከሕዝቡ የመግዛት አቅም በላይ እንዲሆኑ ማድረግ፣ 3ኛ) የሚፈለገው ዕቃ ወቅቱን ጠብቆ ከሚፈለገው ቦታ እንዳይደርስ በማጓተት የሸቀጥ እጥረት በመፍጠር የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተል...ወዘተ 4ኛ) እንደዚህ ተጉላልቶ በሚደርስ ሸቀጥ ላይም ተፈላጊነቱን የተረዳው ነጋዴ በዕቃ ዋጋ ላይ ከአቅም በላይ የሆነ ገንዝብ ሊጠይቅ ይችላል።
ስለዚህ ሸማቹ ሕዝብ ያላግባብ ይጎዳል ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ ህወሓት የምዕራባውያን ታዛዥ በመሆኑ፣ የተባለው ሁሉ ዕውን ላይሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ቢቻልም፣ ውሎ አድሮ የማይቀር ሁኔታ በመሆኑ፣ ከአሁኑ አርቀን ማስተዋል ይገባናል። ወደብ አያስፈልገንም እያለ ሲያውገረግር የነበረው ህወሓት ዛሬ በራሱ ከበርቴዎች ግፊት በኬንያ በኩል የወደብ ፍለጋ ደጅ ጥናቱን ተያይዞታል።
ይህንን የአገራችንን በውጭ መንግሥታት መከበብ የህወሓት አገዛዝ እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል። ህወሓት የኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቀው ባለመሆኑና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር በፍቅር የከነፈ በመሆኑ፣ የውጭ ዜጎች አገር ውስጥ ሕዝባችንን እያፈናቀሉ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን ይዘው ምርታቸውን እንዲያካብቱ መንግሥት ነኝ ባዩ አካል ራሱ በሕግ ፈቅዶላቸዋል።
ህወሓት የተጠመደው ለአገሪቱ ደህንነት ሳይሆን ጧት ማታ ሕዝቡን በማፈን፣ በመግደልና በጎሳ ከፋፍሎ እርስ በርሱ በማፋጀት እኩይ ተግባሩ ላይ ነው። አገዛዙ፣ የአገሪቱን ልማት አሳድገናል፣ መንግሥታችንም ልማታዊ መንግሥት ነው እያለ ቢመጻደቅም፣ አሁን ዓለምን ጉድ ባሰኘ መልኩ ሕዝባችን በረሃብና በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ይገኛል።
ህወሓት የሚከተለውን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ፣ የሃያ ስድስት ዓመታት የህወሓት ሰቆቃና አፈና የወለደውን፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሕዝባዊ መነሳሳት በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ በማኮላሸት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የማይተበትበው ተንኮልና የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሕዝባችን ግን በህወሓት ላይ ያለው ተስፋ ተሟጦ ስላለቀ፣ ከአሁን በኋላ ፀጥ-ለጥ ብሎ ለመገዛት ከማይችለው ደረጃ ደርሷል። በመሆኑም፣ ህወሓት በወታደር ኃይሉና በስለላ ድርጅቱ አማካኝነት ሥልጣኑን ለማስቀጠል ሌት ተቀን እየጣረ ነው። ወታደራዊ ኃይሉና የስለላ ድርጅቱ ምርኮዞቹ ቢሆኑም በአሁኑ ሰዓት እየጎበጡ በመሄድ ላይ በመሆናቸው፣ “ጥልቅ ተሃድሶ “በሚል የማስመሰያ እርምጃ ከሥር ከሥሩ በስለላና በካድሬ ሥራ የተሰማሩትን አነስተኛ ማዕረግ ያላቸውን ወታደሮች ከየክፍለ-ጦሩ በማባረር ላይ ስለሆነ፣ በርካታ ወታደሮች ከሠራዊቱ እየኮበለሉ ከሥርዓቱ ጋር እንዲጣሉና ተቃዋሚ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው። ስለዚህ ሕዝባዊው ተቃውሞ እየጠነከረ እንጂ አገዛዙ እንዳለመውና ተግባራዊ ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰላም እየገዛ አይደለም፤ ለወደፊቱም በዚህ መልኩ ሊቀጥል አይችልም።
በእስልምና እምነት ተከታዮች “የሕገ-መንግሥት” ይከበር ጥያቄ የተጀመረው መነሳሳት በኅዳር 2008 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማን ለማስፋት በሚል የወጣው አወዛጋቢ መርሃ-ግብር የሚያስከትለውን የመሬት ቅርምት ተከትሎ በአዲስ አበባ ዙሪያ የተቀጣጠለውን የኦሮሞ ወጣቶችና አዛውንት መነሳሳት፣ የሐምሌ 2008 ዓ. ም የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አደባባይ ፈንቅሎ እንዲወጣ አደረገው። ይህ ሁኔታ ቀደም ካሉት መነሳሳቶች ለየት የሚያደርገው፣ የጎንደሩ ተቃውሞ የኦሮሞ ወጣቶችን መነሳሳት ደግፎ መነሳቱና የኦሮሞ ወጣቶች ንቅናቄም እንዲሁ የአማራውን ሕዝብ መነሳሳት ደጋፊ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ማረጋገጡ ነው። በቋንቋ ከፋፍሎ ኢትዮጵያን እቆጣጠራለሁ ብሎ ሲያልም፣ እንደ ጦር ሲፈራው የነበረው የኢትዮጵያውያን አንድነት ስሜት በገሃድ መውጣቱ ህወሓትን አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ከተተው።
ምንም እንኳን ከዳር እስከዳር ይፋ የሆነ የሕዝብ መነሳሳት ቢኖርም፣ ጠላትን ማወቅና እንዴትም አድርጎ መታገል እንደሚያስፈልግ ጠንቅቆ ማወቁ ድልን ለመጎናጸፍ መሠረት ነውና፣ ለሀገሩና ለመብቱ ለመታገል ቆርጦ የተነሳው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠላቱን ስልትና የጉዞ አቅጣጫ ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል።
በአንድ እግሩ ቻይና፣ በሌላው ደግሞ በምዕራቡ አገሮች በተለይም አሜሪካ ላይ የቆመው ህወሓት፣ በሰው ልጅ መብት ረገጣ አኳያ እያደረሰ ባለው በደል ምክንያት የምዕራብ አገሮችም እንኳን አቋማቸውን እየመረመሩ ለመሆናቸው ጠቃሽና አመልካች ፍንጮች እየታዩ ነው። የገንዝብና የፖለቲካ ጭንቀቱ ደግሞ ህወሓትን የግድ ወደ ቻይና እንዲያተኩር አድርጎታል። የምዕራቡ ዓለምም አሁን እያሳየ ባለው አቋሙ ከቀጥለ፣ ዋና የብድር ምንጩ የምዕራቡ ዓለም ስለሆነ የገንዘብ አቅሙን ሊጎዳው እንደሚችል ግልጽ ነው። ስለዚህ ህወሓት ከአሥር ዓመታት በፊት የነበረው የእዩኝ እዩኝ አመሉ ከአሁን በኋላ ደብቁኝ ድብቁኝ ሊያሰኘው ይችላል።
የአገሪቱን ልማት አሳድገናል ሲባልለት የነበረው ቀቅቃዛ ውኃ የተቸለሰበት ሽሮ ሆኗል። በልማት ስም በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች ደን እየመነጠሩ ሕዝብን ሲያፈናቀሉ፣ ሆይ! ሆይ! ይባልላቸው የነበሩ የህንድ የእርሻ ኩባንያዎች በደረሰባቸው ኪሣራ ምክንያት የእርሻ ቁሳቁሶቻቸውን በሀራጭ እየሸጡ መውጣታቸው ለህወሓት አስደንጋጭ ዜና ሆኖበታል።

ከአሁን በኋላ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው ሕዝባዊ አመፅ ምክንያት ሌሎች ኩባንያዎች ሊገቡ የሚችሉ አይሆንም። አንድ ኩባንያ በአንድ አገር ውስጥ እጁን ከማስገባቱ በፊት ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር መሆኗን በቅድሚያ ሊያጤነው የሚገባ የመጀመሪያ መመሪያው ነው። በ90ዎቹ፣ ደቡብ አሜሪካ ለልማት በሚል ሰበብ ከአውሮጳና ከሰሜን አሜሪካ በአማዞን ወንዝ ዳርቻ ሲርመሰመሱ የነበሩ አልሚዎች በአካባቢው በተፈጠረ አለመረጋጋት ምክንያት ዕቃቸውን ጠቅልለው ወደ ሌላ አገር እንደሄዱ የሚታወስ ነው። የነበራቸውን ንጥረ-ነገሮች ሁሉ ደፍተው በመውጣታቸውም የአማዞን ወንዝ ተፋሰስ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ እንዲበከሉ ሆነዋል። ይህ ችግር በአገራችንም እየታየ ያለ ሀቅ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ለብዙዎች ሚስጥር አይደለም። በሥልጣን ላይ ያለው ፀረ-ሕዝብ የህወሓት ቡድን በንፁሃን ደም የታጠበ በመሆኑ፣ በምንም ዓይነትና መቸም ቢሆን የሕዝብን ድምፅ እንደማይሰማና እንደማያከበር ግልጽ ነው። ከዚህ ሁሉ ተመክሮ በኋላ የህወሓት አገዛዝ ወዳጅ ወይም ሕግ አክባሪ ነው ብሎ የሚገምት ካለ ለህወሓት ያደረ ወይም የተደነጋገረ፣ አስተዋይነት የጎደለው ሰው ብቻ ነው።
በጎንደር የተጀመረው የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዶ የትግሉን ባህሪ ለውጦታል። በየቀየው በተቋቋሙ በጎበዝ አለቆች የሚመራው ሕዝባዊ ትግል፣ ህወሓት ለሚያደርሰው ጥቃት አፀፋውን መመለስ በመጀመሩ፣ የትግሉ ሂደት ለሃያ አምስት ዓመታት የተከተለውን የተቃውሞ መልክ ለውጦታል።
በዚህ ሁኔታ የተደናገጠው ህወሓት አገሪቱን በቀጠና ከፋፍሎ በራሱ አጠራር “ኮማንድ ፖስት” የተሰኘ ወታደራዊ አስተዳደር በመመሥረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ተገደደ። ይኸው ለስድስት ወራት የወጣው ጊዜያዊ አዋጅ፣ ዛሬ ከስድስት ወራት በኋላም ያው ጊዜያዊ አዋጁ እንደተጠበቀ ነው። በጎንደርና በጎጃም ያለው የትጥቅ አመፅም ጊዜያዊ አዋጁ ሳያግደው እንደቀጠለ ነው። “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ” እንዲሉ፣ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬው ለፓርላማው ባቀረበው ዘገባ “85% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል ጠይቋል” ሲል ተደምጧል። ይህ አባባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም የተሰጠ ሰንካላ ምክንያት እንጂ ሕዝቡ በወታደራዊ አስተዳደር ሥር እንቆይ ብሎ እንደማይጠቅ የታወቀ ነው። ምክንያቱም በየአካባቢው የተሰማራው ወታደር ንብረት ይቀማል፤ ሴቶችን ይደፍራል፤ ከሁለት በላይ ወጣቶች በአንድ ላይ ቆመው ሲያወሩ ያፍናል፣ የፈለጉበት ቤት በድፍረት ገብተው አባወራውን ያዋርዳሉ፤ ቤት ይዘርፋሉ፣ ብዙ ሰዎችን ደብዛቸውን አጥፍተዋል፣ በሚስጥር እስር ቤቶች ውስጥ በርካታ ሰዎችን እያሰቃዩ ነው፣ መላ አገሪቱ እስር ቤት ሆናለች...ወ.ዘ.ተ፣ ወ.ዘ.ተ። ታዲያ ጨዋና ሰላም ፈላጊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን መረን የተለቀቀና ወሮ-በላ ወታደራዊ አስተዳደር ይቆይልን ብሎ ድምፅ ይሰጣል ተብሎ ይታሰባልን? ምናልባት የህወሓት ከበርቴዎች ድምፅ ሰጥተው ሊሆን ይችላል።
ከታሪክ እንደምንረዳው የአንዱ ሽብርተኛ የሌላው ነፃ አውጭ ነውና ለነፃነት የሚታገሉትን ሁሉ ጨቋኝ ኃይሎችና ሽብርተኞች ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። ሰላማዊ ትግል ማለት በህወሓት አገዛዝ ምርጫ ውስጥ መሳተፍና ጠባይን አሳምሮ መገዛት ማለት አይደለም። ከህወሓት የሕግ ድንጋጌ ውጪ ብቻ ሳይሆን በተፃራሪው መንገድ የሚካሄድን ተቃውሞ ይጨምራል። ትግል ሲባል ከተሜው፣ አርሶ-አደሩ፣ ላብአደሩ፣ ታክሲ ነጂው፣ ወንዱ፣ ሴቱ፣ ወጣቱና ሽማግሌው ሁሉ የሚሳተፍበት መሆን አለበት። ይህም ሕዝባዊ መነሳሳት በአገር- አቀፍ ደረጃ መቀናጀትና መተሳሰር ግን አለበት።
የህወሓት አገዛዝ የምርጫ ኮሚሽኑን ለራሱ እንደሚበጅ አድርጐ በቁጥጥሩ ሥር ባዋለበት በአሁኑ ሁኔታ፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማገኘት መጠበቅ ተላላነት ነው። በ2007 ዓ.ም የምርጫ ወቅት መቶ በመቶ አገዛዙ አቸናፊ ሆኖ እንደወጣ ይፋ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በምርጫ አንሳተፍም ማለትም እራሱ ትግል መሆኑም መታወቅ አለበት። በአገዛዙ ላይ ማዕቀብ መጣልና ትብብርን መንፈግ ትግል መሆኑንም መዘንጋት አይገባም። አገዛዙ ያደረገው ገንቢና ተጨባጭ ለውጥ አልታየም፣ ዛሬ ከትናንት ብሷል እንጂ። የህወሓት ምርኩዝ ጊዜያዊ ወታደራዊ ሥርዓቱ አሁንም ቢሆን ያው አፈና፣ ጭፍጨፋ፣ እስርና ግድያ ያለማቋረጥ በማካሄድ ላይ ነው።
ሕዝባዊ መነሳሳቱን ለማፈን ይበጀኛል ብሎ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በራሱ ላይ ተመልሶ ማነቆ እየሆነበት መሆኑ እየታየ ነው። የሕዝብን ከቦታ ቦታ መዘዋወር ለመቆጣጠር የአቋቋመው የኬላ ፍተሻ፣ የአገሪቱን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እያነኳኮተው ነው። ሰዓታት በሚፈጀው ፍተሻ ምክንያት የንግድ ዕቃዎች ከቦታ ቦታ በተፈለገው ፍጥነት አይደርሱም።
ህወሓት ሁኔታዎች ሲጠጥሩበት የሕዝቡን አመፅ ለማዘናጋት በካድሬ ቄሳውስት ታቦት አስይዞ ለእርቅ እየተማጸነ ነው። ምንነትቸውንና ማንነታቸውን እያንቋሸሸ እንዳላፌዘባቸው ሁሉ ዛሬ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችን እባክችሁ አማልዱኝ እያለ ነው። ሁለንተናው የማይጨበጥና ነገረ-ሥራው ሁሉ የማይያያዝ፣ ከብርሃን በፈጠነ ሁኔታ አቋሙ የሚለዋወጥ አሳይ-መሲህ የገዥ ቡድን በአገራችን ከተፈጠረ እነሆ አንድ ትውልድ ተቆጠረ። ሕዝብ ከእንግዲህ ምን ይጠብቃል? በቃ፤ ብሎ ቆርጦ ቢነሳ የሚገርምና የሚደነቅም አይደለም። እባብ ቆዳውን በየወቅቱ ቢያወልቅም በመጨረሻ ከሞት አያድነውም። የህወሓት የአገዛዝ ሥርዓትም እንደዚሁ ውድቀቱ አይቀሬ ነው። ይሁን እንጂ የተለሳለሰ ትግል የትም አያደርስምና የሕዝብን የመከራ፣ የበደልና የስቃይ ጊዜ ለማሳጠር ዓይነተኛውና ብቸኛው መንገድ የተባበረ የሕዝብ ትግል ነው። የሕዝብ ክንድ መላላትና መዛል የለበትም። ሕዝባዊ ድል አቀናጅቶ መታገልን ይጠይቃል። ትግሉ እንዴት ይመራ ለሚለው፣ ሀገራዊውን ተጨባጭ ሁኔታ ከአካባቢውና ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር አዛምዶ በመመርመር የመፍትሄ መንገድ ይገኛል።
የራሳችንን ታሪካዊ ቅርስና የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በሚመራን የትግል ስልት ለመሰማራት የማንንም ፈቃድ ጠያቂ መሆን የለብንም። የህወሓትን አገዛዝ አስወግዶ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለማዳን፣ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ትግል ማስፋፋትና ማጠናከር አለጥርጥር ለድል ያበቃል።
ኢሕአፓ (አንድነት) አገራችን በውጭም ሆነ በውስጥ ጠላቶቿ ተሰንጋ ከተያዘችበት ችግር ለማላቀቅ ፍቱን መድኃኒቱ ሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታቸውን ወደጐን በመተው፣ የጋራ በሆኑ አንኳር አንኳር ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ተስማምተውና አንድ ሆነው ሲታገሉ ብቻ ነው ብሎ ያምናል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን አገራችንን አሁን ካለችበት የአዞ መንጋጋ ማውጣት አይቻልም፣ አገራችን ለሚደርስባት ወድቀት ተጠያቂዎች እንደምንሆን መረዳት ያስፈልጋል።

አገራችንን ከጥፋት ለማዳን ታሪካዊ ግዴታችንን እንወጣ!

Last modified onTuesday, 30 May 2017 11:26
back to top