Menu

ያበደ ውሻ እየተናከሰ ይሞታል

ከአምባገነን አገዛዝ ጥይት እንጂ ዴሞክራሲ አይጠበቅም። ዘረኛውና አምባገነኑ ህወሓት ሥልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮ ከሃሳቡና ከሚከተለው ፍልስፍና የተለዩትን ሁሉ እየገደለ፣ ሰውነታቸው ትል እስኪያፈራ ድረስ በቁም በጨለማ ጉድጓድ ውስጥ እየቀበረ እንዲሞቱ ያደረገ፣ በሕይወት ተርፈው የተፈቱትም በደረሰባቸው የሞራል ስብራትና ስቃይ ምክንያት ጤናቸው ተቃውሶ ከሞቱት ባላነስ መልኩ እንዲኖሩ ያደረገ ግፈኛ ቡድን ነው። የህወሓት የገዳይነት ባህሪ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከመነሻው ተክኖበት የመጣ ስለሆነ የጭካኔ ባህሪው ከዚህ ጎልቶ ቢወጣ የሚደንቅ ሊሆን አይገባም። የህወሓት ቡድን ስንት ብርቅዬ የኢትዮጵያን ልጆች እየበላ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚያውቁት ሃቅ ነውና።

ህወሓት የተቃወሙትን የትግራይ፣ የጎንደር፣ የወሎና የሌሎችንም አካባቢዎች ሕዝብ እየዳመጠ ነበር አዲስ አባባ የገባው። ኢትዮጵያን የሚያጠፋ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው ብለው የተቃወሙ የፖለቲካ ድርጅት አባላትን አፍኗል፣ ጨፍጭፏል። በትረ-ሥልጣኑን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በጠራራ ፀሐይ የፈጀውን ሕዝብ ቤት ይቁጠረው። በአገሩ ላይ የመኖር የዜግነት መብቱ ተገፎ እንዲሰደደ የተደረገውን ሕዝብ ወላድ ይቁጠረው። በአገራችን ታሪክ አንድ ሰው እስረኛ ከሆነ ሕጋዊ ፍርድ ተሰጥቶት ፍርዱን ይቀበላል እንጂ ያለፍርድ በጥይት እየተደበደበ በእሳት እንደበግ መስዋዕት የሚለበልብ የህወሓት አገዛዝ ብቻ ነው።

ይህ ጨካኝ ዘረኛ አገዛዝ በጎንደር፣ በጎጃምና በኦሮምኛ ተናጋሪ አካባቢዎች ከፍተኛ የጀምላ ጭፍጨፋ ያለማቋረጥ እንደሚያካሄድ ቀን በቀን የምንሰማውና የምናየው ሃቅ ነው። ዛሬ ደግሞ የኢሪቻን በዓል ምክንያት በማድረግ በበዓሉ ቦታ በተገኘው ሕዝብ ላይ በአንድ ቀን ከ300 ሰዎች በላይ ሕዝብ መፍጀቱ እጅግ የሚያስቆጣና የሚዘገንን አረመኒያዊ እርምጃ

ነው። በማንኛውም አገር ሕዝብ ተበድያለሁ ካለ አቤቱታውን የሚያሰማውና መብቱ እንዲከበርለት የሚጠይቀው በሥልጣን ላይ ለሚገኘው መንግሥት ነው። በአገራችን የፍትህ ያለህ እያለ ለሚጮኸው ሕዝባችን በደልህ ምንድነው? ብሎ የሚጠይቀውና ለጥያቄው መልስ ሊሰጥ የሚችል አካል የለም፣ ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክል መንግሥት አይደለምና። ስለሆነም የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ፍላጎት፣ አቅምም ሆነ ችሎታው እንዲሁም የሞራል ብቃትም የለውም። ህወሓት ለራሱ ሥልጣንና ለሥልጣኑ አጋፋሪ ለሆኑ ጥቂት ግብረ-በላዎች የሚያገለግል በመሆኑ የሌላውን ሕዝብ መብት የሚያዳምጥ አይደለም። ሊያዳምጥም አይችልም፣ ባህሪውም ሕዝባዊ አይደለም።

አምባገነን አገዛዝና የተነቃነቀ ጥርስ ተነቅሎ ካልወጣ ጤና አይሰጥም። ዛሬ በደብረ ዘይት/ቢሸፍቱ በህወሓት ጥይት የወደቁ ጀግኖች የነፃነት ሰማዕታት ናቸው። ትናንት በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በደብረማርቆስ፣ በተለያዩ አሮምኛ ተናጋሪ አካባቢዎችና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ህወሓትን ተቃውመው ለመብትና ለዴሞክራሲ ሲታገሉ የወደቁ ጀግኖች ሰማዕቶቻችን ናቸው። ታጋይ ይሞታል ትግሉ ግን አይሞትም ብለው ከጎናቸው የሚወድቁትን እህትና ወንድሞቻቸውን ሬሣ ለህወሓት አንሰጥም በማለት በጀግንነት ከወደቁበት አንስተው የሚወስዱና የሚዋደቁ የዴሞክራሲ መብት የጠማቸው ኢትዮጵያውያንን አይዟችሁ ብለን ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።

ይህን አረመኔ አምባገነን አገዛዝ አስወግዶ በምትኩ ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሁላችንም በእኩልነት ተከባብረን የምንኖርባት ኢትዮጵያን መመሥረትና መገንባት የምንችለው በትግሬነት፣ በአማራነት፣ በኦሮሞነት፣ በደቡብነት፣ በሐረሪነት...ወዘተ ተከፋፍለን ሳይሆን በአንድነት በመቆም ለሚፈለገው ግብ በርትተን ስንታገል ነው። እየተለያዩ መታገል ለዘረኛው ህወሓት አመቺ በመሆኑ ለነገ ሳንል ዛሬውኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ እንድንታገል ኢሕአፓ (አንድነት) እነሆ ጥሪውን ያስተላልፋል።

የተቃዋሚ ኃይሎች አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ በአንድ ላይ ቁመን ሕዝባችንን በጠራራ ፀሐይ እየጨፈጨፈ ያለውን ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ በጋራ እንድንታገል ኢሕአፓ (አንድነት) አስቸኳይ ጥሪውን ያቀርባል። ጊዜው አሁን ነው። በየተራ እየተነሳን፣ በየተራ መሞታችን ማብቃት አለበት።

ኢሕአፓ (አንድነት) በደብረ ዘይት/በቢሸፍቱ፤ በተለያዩ የኦሮምኛ ተናጋሪ አካባቢዎች፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በኮንሶና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ቤተሰቦቻቸው በግፍ ለተገደሉባቸው ቤተሰቦች ሁሉ እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጥልን እያለ የተሰማውን መሪር ሃዘን ይገልጻል።

ድል ለሰፊው ሕዝብ!

Last modified onTuesday, 04 October 2016 15:06
back to top