Menu

የኢትዮጵያ ድንበር እየተቆረሰ ለጉርብትና የሚሰጥ ገጸበረከት(ዳረጎት) አይደለም

ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያውያን መስዋእትነት ተከብሮ የኖረው የኢትዮጵያ ድንበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር በቀል በሆነው የውጭ ሃይሎች አገልጋይ ህወሃት/ኢሕአዴግ የተባለ ቡድን በብሔር ስም አገራችንን በታትኖ ለሚመሰርተው ጎጠኛ መንግስት ድጋፍ ለመሰብሰብ ሲል ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ እየተረካከቡ የኖሩበትን በቁመቱ 1600 ኪሎሜትርና ስፋቱ ከ40-60 ኪሎሜትር የሆነ ለም መሬት “ለታላቋ ትግራይ” ምስረታ ዓላማ ገና ከጅምሩ ለተባበረችው ሱዳን አሳልፎ ለመስጠትና ድንበር ለመካለል ሽር ጉድ እያለ ነው። “የታላቋን የትግራይ”ን ክልል ለማስፋት ሲባል ኩታገጠም የሆነውን የጎንደርንና የወሎን ክፍለ አገር ሰፊና ለም መሬት በጉልበት የትግራይ ክልል ውስጥ ቀላቅሎ ሕዝቡንም ከሚናገራቸው ቋንቋዎች በአንደኛው ፣በትግርኛው ምክንያት ካለሕዝቡ ምርጫና ፍላጎት በማጠቃለልና በማስፈር በሕዝብ መካከል መቃቃርና ቋሚ ግጭት ለመፍጠር በትጋት ቀጥሎበታል።በምስራቁም ቢሆን ሶማሌዎች ይገባናል ብለው ከኢትዮጵያ ጋር በተደጋጋሚ ጦርነት የከፈቱበት ጥያቄ በመሆኑ ጠንከር ያለ የሶማሊያ መንግስት የለም እንጂ ቢኖር ለመፈራረም ወደዃላ አይልም፤የኦጋዴን ነጻ አውጭ ነኝ የሚለው ተገንጣይ ሃይል ፈርጠም ካለ የሚጠይቀውን የኢትዮጵያ ግዛት ገንጥሎ ከሶማሊያ ጋር ለመቀላቀል ወይም የራሱን ክልል መንግስት ለማቋቋም በውጭ አገርና በወያኔ ሚስጥራዊ ድጋፍ ጭምር ሁኔታው ከቀን ወደቀን እየተመቻቸለት ነው።በኬንያም በኩል ቢሆን የይገባኛል ጥያቄ ቢነሳ የኢትዮጵያ ሞያሌን አሳልፎ ለመስጠት ህወሃት/ኢሕአዴግ አይግደረደርም። ጅቡቲም ደፍራ የአፋር መሬት ይገባኛል ብትል ህወሃት ቆርሶ ከመስጠት አይመለስም። በመሃል አገርም ውስጥ የተለያዩት ተገንጣይ ሃይሎች ከበረቱ፣ጭራሽ ለመቆጣጠርና ለመግዛት የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ “ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ” በማለት ሕዝቡን ከቀውስና ከእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከተው ወደአዘጋጁት ቦታ ለመሄድ ለህወሃት/ ኢሕአዴግ መሪዎች አይከብዳቸውም። “የታላቋ ትግራይ” ሕልም እውን ከሆነ የሌላው መኖር አለመኖር አያስጨንቃቸውም።

 የክልል ጥያቄ ሌላ መልክ እየያዘና እየተካረረ መጥቷል።በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚታየው የአላስነካም ትግል የዚህ አንዱ አካል ነው።የትግሉ አዝማሚያ ሲመረመር በኢትዮጵያ አንድነትና በዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ዙሪያ ሳይሆን የማንን መሬት ማን ይወስዳል የሚል ጎሳና ክልል ተኮር የሆነ ተቃውሞ ነው።ወያኔ በቀየሰው መንገድ ኢትዮጵያን በጎሳና በክልል ለያይቶና ሸንሽኖ ለመበታተን የሚደረገውን ማንኛውንም ጸረ አንድነት ንቅናቄ ሸንጎ ይቃወማል፤ይታገላልም። ከሁሉም በፊት ግን የጎሳ ፖለቲካና እንቅስቃሴ ለማንም እንደማይበጅና ሁሉንም የሚጎዳ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ እየገለጸ ትግሉ ሁሉን ያቀፈና ያሳተፈ ለጋራ ጥቅም መሆን እንደሚገባው ይገልጻል።

በህወሃት/ኢሕአዴግና  በሱዳን መካከል የሚደረገውን የድንበር ውል እንደማይቀበለውና ይህን በውጭ ሃይሎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፈራረስ ተንኮል በዝምታ እንደማይመለከተውና እንደማይቀበለው እየገለጸ በድንበር ኮሚሽን የቀረበውን ታሪካዊ ማስረጃና የባለቤትነት ጥያቄ ከልብ ይደግፋል።በሚፈለገው ቦታ አብሮ ለመቆም ዝግጁ ነው።     

በሌላውም ያገሪቱ ክፍል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመቀጣጠል ላይ ነው።የክልል ዓላማ ከሚያስተናግዱት ጎን ለጎን በኢትዮጵያዊነት ፣ለኢትዮጵያ አንድነት፣ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን፣ለሕግ የበላይነት የሚታገሉትም በተለያየ መንገድና ቦታ በሚችሉት መንገድ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።ከነዚህ ጋር ሸንጎ የትግሉ አካል መሆኑንና አብሯቸው እንደሚሰለፍ ሊገልጽ ይወዳል።

በየአቅጣጫው እየተካረረ የመጣው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሁለት ዓይነት ክስተቶችን ሊወልድ ይችላል።

1ኛ.የጎሰኞች እንቅስቃሴ ከተጠናከረና የአንድነቱ ሃይል ከተዳከመ ኢትዮጵያ የመገነጣጠል ዕድሏ ከፍተኛ ይሆናል።

2ኛ.የአንድነት ሃይሉ ከተሰባሰበና እንደ ሃይል ከወጣ የሚፈራው አደጋ ሊቀለበስ ይችላል።

የኢትዮጵያ መገነጣጠል ለማንኛውም ቢሆን የሚሻልና የሚጠቅም አይሆንም። ትርፉ ይበልጥ ደቃቃና ደካማ ሆኖ ለውጭ አደጋ መጋለጥና ከድህነት ሳይወጡ እርስ በርሱ በድንበር ምክንያት፣በማያባራ ግጭት ውስጥ መኖር ነው።

ለሁሉም ጠቃሚና የሚሻለው መንገድ ሃይልን አስተባብሮ የጋራ ጠላትን አሶግዶ በአንድ አገር ልጅነት፣በኢትዮጵያዊነት ተከባብሮ  የሚኖሩበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስፍኖ ለመኖር በጋራ መታገል ነው። ለዚህ የጋራ ድል በተለያየ ብሄርና በፖለቲካ ድርጅት ስም ተነጣጥለው የሚታገሉት አንድ ላይ ሆነው የጋራ መመሪያ በማውጣት ትግላቸውን የሚያቀናጅ አካል መፍጠር ይኖርባቸዋል። ጊዜውም አሁን ነው።ያ የሚፈጥሩት አካል ወያኔ በተወገደ ማግስት የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚረዳ መሠረት ሊሆን ይችላል።ከዚህ ውጭ በያዙት መንገድ ከቀጠሉ ማንም ያሰበውን ሳያገኝ ባለው ጨቋኝ መንግስት ወይም ከሱ ባልተለዬ አዲስ መጥ ዘረኛና አምባገነን ቡድን ሲደሙ ከባሰም ኢትዮጵያ ተበታትና  አገረ ቢስ ሆኖ በያገሩ ተሰዶ መኖር ይሆናል።

ጊዜው ከመምሸቱ በፊት አሁን በረፋዱ ሰዓት የግል ፍላጎትን ትቶ በጋራ ፍላጎት ላይ ማተኮር ይገባል። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ ) በአገር ቤትና በውጭ አገር የሚታገሉት ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ ተሰብስበው አገራችንን ለገጠማት ችግርና አደጋ መልስ መስጠትና ለአገር አድን ተጋድሎ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጥሪ እያደረገ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል። 

ኢትዮጵያ በአንድነት ለዘላለም ትኑር!

Last modified onThursday, 12 May 2016 11:00

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.

back to top